ጥያቄ?

News

ጥያቄ ?

እህቶቻቸን እየታደኑ ጓደኞኛችን እየታፈኑ

ቀማኞች በየቦታው ሰው በፍርሃት ሲያባንኑ

በሺዎች ብር ሲጠይቁ ከተሳካ ሲቀበሉ 

ካልተከፈለ ሲገደሉ

ይህን እያዩ ወንዶች ወዴት ገቡ የት ኣሉ?

ሴት ልጆች ሲሰቃዩ ሲገደሉ በየቦታው

ኣይኑ እያየ ዝም የሚለው ወንዱ ሁሉ ምን ነካው?

ሽፍቶች አገሯን ሲሞሏት ወንዶቻችን የት ገቡ?

እህቶቻቸዉ ሲሞቱ እናቶቻቸዉ ሲያነቡ

በኣሰቃቂ ወንጀለኞች ኣገሩ ሁሉ ተጥለቅልቆ

ሰዉ እንደልቡ እንዳይላወስ በፍርሃት ተሸማቆ

ወንዱ ፀጥ ኣለሳ ምነው ወይስ ሄዷል ኣገር ለቆ?

በጭንቁ ትግል ጊዜ ኣብራ ታግላ ኣብራ ዘምታ

ከቤት የቆየችውም ተሰቃይታ ክብሯን አጥታ

ያ ቁስሏ ገና ሳይሽር በኣገሯ ወንዶች ስትታደን

ተወልዳ ባደገችበት ህይወቷ በከንቱ ሲመክን

ወንዱ ሁላ የት ገባ ይቺ እህቱን የማያድን?

ርህራሄ ኣልቦ ሽፍታ ሁላ ኣገር መሬቱን ሲረብሽ

ቆንጮራና ጩቤ ይዞ ሰው እንደትቢያ ሲያንቋሽሽ

የኣገር መንግስታቱ የት ሄዱ ፖሊሶቹስ ወዴት ሸሹ

ወሮበሎች ቀን ከማታ የሰው ሃብት ሲያሟሽሹ

የህብረተሰቡን ኣኗኗር ባህሉን ሲያበላሹ

ህግ ኣልቦነት ሲንሰራፋ ሴቶች በፍርሃት ሲርዱ

ቤተሰቦች በሃዘን ጨርቃቸውን ጥለው ሲያብዱ

መልካም ወንዶች የት ኣሉ እህቶቻቸዉ ሲታረዱ?

ተቆጣጣሪውስ ማነው ዳኛውስ የታል ፍርዱ?

ህግ ኣክባሪ ወንድ ሁሉ ስሙ ሲጠፋ ዝም ኣለሳ

እህቱ ህይወት ኣጥታ እናቱ ደም ኣልቅሳ?

በግፍ ለተገደሉት እህቶች መታሰቢያ እየሩ: 

እየሩ (JB)

22/6/2024

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *