የፖለቲካ ትንተና ወይስ መወድስ ቅኔ?

Articles

ከጥዑመ ልሳን አድማሱ

በአንድ ወቅት አንድ ወንድሜ ቪዲዮ ልኮልኝ ስመለከት ድንገት ዓይኔ በአንድ ዝግጅት ላይ አረፈ። ይህም ዝግጅት የአቶ በቀለ ገርባንና የአቶ ጃዋር መሃመድን የዋሽንግቶን ጉብኘት አስመልክቶ የተዘጋጀ የ’ገለልቱማ’ መድርከ ነበር፡፡

በወቅቱ መርሃግብሩን የሚመሩት ግለስዎች ይጠቀሙበት የነበረው ቅዋንቅዋ ጉራማይሌ ስለነበር፤ ማለትም የመነጋገሪያ አርእስቱም ሆነ ተነጋሪዎችን ያስተዋውቁ የነበረው አንዴ በአፋንኦሮሞ፡ ሌላ ጊዜ በአማርኛ፡ ሲያሰኛቸው ደግሞ በፈረንጅኛ ስለነበር፡ የመርሃግብሩን አካሄድም ሆነ ይዘት በውል ለማጤን አዳጋች ነበር። ቢያንስ እኔ በሁኔታው በጣም ከመደናግሬ የተነሳ የሁሉም ተሳታፊዎች ንግግር በአግባቡ መከታተል አልቻልኩም ነበር።

ስለሆነም፤ የተናጋሪዎቹን ማንነትም ሆነ የመልእክታቸውን ጭብጥ ገብቶኝ የተከታተልኩት በአማርኛ ይናገሩ የነበሩትን ተሳትፊዎች ብቻ ነበር፡፡ በተለይም በአትኩሮት ያዳመጥሁት፡ የአቶ መስፍን አየነውን እና የአቶ ያሬድ ጥበቡን ነበር።

በመጀመርያ ወደ ዋናው ነጥቤ ከመግባቴ በፊት አንድ ቀልቤን ስለሳበው ነገር ነጥብ ማንሳት እፈልጋልሁ፤ ይኸውም፡ ያዘጋጆቹ የግዜ አበጃጀት ነበር። ማለትም፡ የውይይቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በግል ወይም ድርጅታቸውን ወክልው ለመጡት ታዳሚዎች የተሰጠውን የግዜ መቁነን በሚመለከት ነው። እንደ የመድረኩ መሪዎች አገላለጽ፤ ለያንዳዱ ተናጋሪ የተሰጠው ጊዜ ሶስት ደቂቃ ያህል ነበር። ታድያ ፈረንጆቹ እንደሚሉት “ሳውንድ ባይት” ካልሆነ በስተቀር በዚህ ባጭር ጊዜ ውስጥ የተምዋላ መልእክት ማስተላለፍ ይቻላል ብሎ ለማመን አዳጋች ነበር፡።

ታዳሚዎቹ የተጋበዙት አንድም የእለቱን ዝግጅት ለማዳመቅ፤ አለያም፡ እነ አቶ ጁሃርን እንክዋን ደህና መጣችሁ ከማለትና ግንባራቸውን ከማስመታት በዘለለ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ምን ዓይነት መልእክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይታሰባል? ይህ ካልኩ በህዋላ ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስ።

አቶ መስፍን፡ በንግግራቸው መግቢያ ላይ እንደጠቀሱት፤ ወደ ስብሰባው የመጡት፡ የትግራይን ማህበረሰብ ወክለው እንዳልሆነና፡ እንደ ትግራዋይነታቸው፤ ባለፉት ሃያ ወራት ጊዜ ውስጥ በትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰውን ግፍ፡ ስቃይ እና ከስብእና ውጭ የሆነውን በደል በማውሳት ለስብሰባ ተሳታፊዎች ለመግለጽ እንደ ነበር ጠቁመዋል። ከዛም ንግግራቸውን ቀጥለው ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል እንደተናገሩ፤ ውይይቱን ይመሩ የነበሩት አስተናባሪዎች፡ ተናጋሪው ንግግራቸውን እንዲቅዋጩ መወትወት ጀመሩ። በመጨረሻም፡ አቶ መስፍን ሊሉት የፈለጉትን ሳይሉ ከመድረኩ ወረዱ። ይህ ሁሉ የሆነው ከአምስት ደቂቃዎች ባልበለጠ ግዜ ውስጥ እንደነበር ያጤነዋል።

የአቶ መስፍን ንግግር፡ አቶ ጃዋርም ይሁን አቶ በቀለን ያላማኮሸ እና በኦሮሙማ ዙሪያ የማያጠነጥን ስለነበር፡ አዘጋጆቹን ጨምሮ የብዙዎቹን ቀልብ ሊስብ ያልቻለ እንደ ነበር በአዳራሹ ውስጥ ሰፍኖ ከነበረው ድባብ መገንዘብ ይቻል ነበር። ለዚህም ይመስላል አቶ መስፍን ከሌሎቹ ተናጋሪዎች በተለየ መልኩ ንግግራቸውን ባጭሩ እንዲገቱ የተደረገው። (ለንጽጽር እንዲያመች፤ አቶ መስፍን ለአምስት ደቂቃዎች ያህል እንደተናገሩ ሲያቆሙ፡ አቶ ያሬድ ግን ከአስራ አምስት ደቂቃዎች በላይ እንደተናገሩ ይገመታል።)

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ ተጋባዦቹ የተጋበዙበት ዋናው ዓላማ ምን ነበር የሚለውን ነው? ስለመጡበት አካባቢ እንዲናገሩ፤ ወይስ ስለ እነ አቶ ጅዋር ጉብኝትና የ’ገለልቱማን’ መድረክ ለማዳመቅ ነበር ? መልሱ የመጀመሪያው ነው ከተባለ ደግሞ፤ ታዲያ በጊዜ አመዳደቡ ላይ የታየው ንፉግነት ለምን አስፈለገ ወደሚለው ሌላ ጥያቄይመልሰናል።

እንዲህም ሲባል የመርሃግብሩ መሪዎች፡ የንግግሩ ይዘት ደስ ሳይላቸው ሲቀር ወይም የጊዜ እጥረት ሲያጋጥም የምደባ ሽግሽግ ማድረግ ወይም ንግግሩ እንዲቅዋረጥ ማድረጉ ያልተለመደ ክስተት ነው ለማለት ሳይሆን ፤ ለምን ያለውን ጊዜ ከታዳሚዎቹ ቁጥር ጋር ተገናዝቦ ሲያበቃ፤ ለተናጋሪዎቹ በቂ ጊዜ መመደብ ሳይቻል ቀረ ነው። ወይስ የግብዣው ዓላማ፤ ከጅምሩም ቢሆን የታዳሚዎቹን መልእክት ባግባቡ ለማዳመጥ ሳይሆን ለዝግጅቱ ድምቀት ሲባል ነበር ማለት ነው?

እንዲህም ስል፡ አቶ መስፍን ፡ በትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ግፍ፤ መከራ እና ስቃይ ሲዘረዝሩ፤ እንደዚሁም ደግሞ፡ ሴቶችንና ልጃገረዶችን በመድፈር እና በምግብና መድሃኒት እጦት፡ ህዝብን እያመከኑ ያሉት ነውረኞችን ሲያወግዙ፡ ለምን ቤቱ በጭሆትና በጭብጨባ አልተናወጠም ማለቴ አይደለም።

እያልኩ ያለሁት፤ በትግራይ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ከበባ፡ በዚሁም ሳቢያ፡ የተከሰተው የምግብ እጦትን፤ የመድሃኒት ጭራሽ መጥፋትን፤ የመብራትንና ስልክ መቁዋረጥን እና የባንክ መዘጋትን በሚመለከት፤ ተናጋሪው የሚያስተላልፉትን መልእክት በጥሞና ማዳመጡ ለምን እንዲህ አስቸጋሪ ሊሆን ቻለ ነው። በእርግጥም እንደተመለከትነው፤ አቶ መስፍን፤ የጀመሩትን አረፍተነገር ሳይጨርሱ፡ ከመናገሪያው ሰገነት በጥድፊያ እንዲወርዱ የተደረገው፤ ድሮውንም ቢሆን ተናጋሪው የተጋበዙት ለይስሙላ ያህል እንጂ፡ ትግራይ ውስጥ የሰፈነውን ችግር የሚገልጸው ንግግር፤ አዳምጦ የመፍትሄው አካል የመሆን
እቅድም ሆነ ፍላጎት እንዳልነበረ ያሳያል።

በዚሁ አንጻር ደግሞ፤ ለአቶ ያሬድ ጥበቡ የተደረገላቸውን አቀባበልና የተሰጣቸውን የጊዜ መጠን፡ ለሌሎቹ፤ በተለይም ለአቶ መስፍን ከተለገሳቸው እጅግ የተለየ እንደነበር እናያለን። ይህም ሊሆን የቻለው በአቶ ያሬድ ስበእና ወይም ማንነት ሳብያ ሳይሆን፡ ያስተላለፉትን መልእክትና የመልክቱን ይዘት በተመለከተ እንደነበር ለመገንዘብ አዳጋች አልነበረም።

አቶ ያሬድን፡ በግል አላውቃቸውም ፤ እንዲሁ በዝና ግን፡ ቀደም ሲል የመ.ኢ.ሶ.ን አባል እንደነበሩና ባሁኑ ጊዜም ከወቅቱ የአገሪቱ የፖለቲካ ተዋንያን አንዱ እንደሆኑ እገምታለሁ። በተለይ ደግሞ፤ “ኦ ሮ አማራ” የሚለውን ሐረግ ለህዝብ ያስተዋወቅኩት እኔ ነኝ፡ ማለታቸውን ስሰማ የነበረኝን ግምት አጠናክሮልኛል። ከዚህም በመነሳት፤ የሚያደርጉት ንግግር በወቅቱ ሁኔታዎች ላይ የሚያነጣጥርና የጊዜውን ተጨባጭ ሁኔታ
ያጋናዘበ በሳል የፖለቲካዊ ትንታኔ ይሆን ይሆናል የሚል ተስፋም ግምትም ነበረኝ።

ማዳመጥ የቻልኩት ግን ከጠበቅሁት ፍጹም የተለየ ነበር። ንግግራቸውን ጀምረው የጨረሱት አቶ ጁሃርን በማመስገን፤ በማሞካሸት እና በማወደስ ነበር። ለዚህም ነበር” የአቶ ያሬድ ንግግር፤ “የፖለቲካ ትንታኔ ወይስ የመወድስ ቅኔ!” እንድል የተገደድክት። በየማህበራዊ ሚዲያው እንደሚደመጠው ከሆነ፤ የአቶ ጃዋር ወደ ስልጣን መድረኩ ለመውጣት እየተቃረቡ ያሉ ይመስላል። ታድያ፤ የአቶ ጥበቡ ማሽቃበጥ፤ መሞዳመድ እና
ለአቶ ጁሃር መወድስ ቅኔ መዝረፋቸው ፡ የአቶ ጁሃርን በስልጣን ኮረቻ ላይ መቆናጠጥ እውን ሲሆን “ተዘከረኒ በመንግስትክ” ለማለት ፈልገው ይሆን?

በእርግጥ ይህ ምንም ዓይነት ጥናት ሳያካሂዱ ወይም ምንም ማስረጃ ዋቢ ሳያደርጉ፤ ተቻኩሎ መሪዎችን ወይም በጥቅሉ ሰዎችን በተጋነነ መልኩ የማመስገኑም ሆነ የመኮነኑ አባዜ እንደ አቶ ጥበቡ ሌሎችንም የፖለቲካ ተንታኞች እየተጠ ናወታቸው ለመሆኑ ብዙ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

‘አስቀድሞ ማመስገን ህዋላ ለማማት ያስቸግራል’ የሚለውን አባባል በውል ሳያጤኑ፤ በየወቅቱ ብቅ ለሚሉት መሪዎች የማይገባቸውን ክብር፤ ሞገስ እና አድናቆት መቸር እና በህዋላም ሰዎቹ የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ሳይሆኑ ሲቀሩ፤ ማፈርና ‘እንዲህ አልመሰለኝም ነበር’ በማለት ቀደም ሲል የሰነዘሩትን ጉንጭ አልፋ አስተያየት ለማስተባበል ሙከራ ማድረጉ የተለመደ ክስተት ሆንዋል።

ለምሳሌ፤ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ መጀመርያ ወደ ስልጣን እንደመጡ ፤ ከብዙዎቹ የፖለቲካ ተንታኞች፤ ሃያሲያን፤ ሙህራን፤ የኪነጥበብ ሰዎች፤ ደራሲያን እና ፖለቲከኞች ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሰጡት የነበረው ሙገሳ፤ አድናቆት እና ክብር ምን ያህል የጦዘ እንድነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

አንዳንዶቹ እስራኤላዊያንን ከባርነት ነጻ ባወጣው በሙሴ ሲመሱልዋቸው ሌሎች ደግሞ ከኖህና መርከቡ ጋር ያነጻጽሩዋቸው ነበር። ከዛም አልፎ፡ ከክርስቶስ ጋር ለማመሳሰል የሚዳዳቸው ሰዎችም እንደነበሩ የሚዘነጋ አይደለም። ይሁንና፤ ‘ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ’ እዲሉ፤ ያሁሉ ክብርና አድናቆት የተቸራቸው “ታላቁ መሪ” ከዛ ከነበሩበት የክብር ማማ ተንከባልለው ታች በመውረድ፤ እንዳልሆኑ በሆኑበት፤ ባሁኑ ወቅት በምንና በማን እየተመሰሉ እንዳሉ ሁላችንም እያየንና እየሰማን ነው። ስለሆነም፤ በየትኛውም ሁኔታ፤ በማንኛውም ሰው ላይ የሚደረገው ትችት፤ በተለይም ባመራር ላይ ላሉት ሰዎች(መሪዎች) የሚሰጠው ውዳሴ፤ ሙገሳና አድናቆት ወይም ነቀፋ፤ ውግዘትና የስም ማጠልሸቱን ኩነት ሚዛኑን ያልጠበቀ፤ ያልተማከለና ዋልታረገጥ ሲሆን፤ በህዝቡ ስነልቡና፤ ማህበራዊ እውነታ እና የግንዛቤ ፍሰት ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ ይሆናል።

ይህም ማለት፤ በየጊዜው ከሚታየውና ከሚሰማው የአድርባይነት፤ የአጎብዳጅነትና ያሽቃባጭነት ጠባይ እና ለባለጸጋውና ለባለስልጣኑ ከሚደረገው የተጋነነ ሙገሳና ውድሴ ከንቱ የተነሳ፤ ማህበረሰቡ በመሪዎቹና በሊሂቃኑ ላይ የነበረውን እምነት እንደሚሸረሸር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ስለዚህ፤ የህዝቡ ትእግስት ተምዋጦ ከማለቁና በህዝቡና በሊሂቁ መካከል ያለውን መስተጋብር ከመፋለሱ በፊት፤ ከወዲሁ ለዚህ ዓይነቱ ብልሹ ልምድ መፍትሄ ሊፈለግለት ይገባል የሚል እምነት አለኝ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *