የምን እናት ኣገር

News

*የምን እናት ኣገር*

እናት ፍቅር ሰጪ
መጋቢና ኣዋቂ
ኣገር ደሞ ደጀን
ድምበርን ጠባቂ

ይመስሉኝ ነበረ
ኣንድ ላይ ሲሆኑ
እናትኣገር ብለው
ዜጐች ሲጀነኑ

የኔዋ እናት ኣገር
ቤት ድምበሬን ከፍታ
ኣሰጨፈጨፈችኝ
ጠላት ኣስገብታ

ሮጬ የማመልጥበት
ጐጆየና ቤቴን
በእሳት ኣጋየችው
ገደለቻት ልጄን
ኣርዳ በላች ከብቴን
ስደት ከተተችው
ያስተማርኩት ልጄን

ቤተ እምነቴን ደፍራ
ጧሪ ልጄን ቀብራ
ማሳየን ኣቃጥላ
ሞፈሬንም ሰብራ

ይቺ ምን እናት ናት
ምን ኣይነት ኣገር
ምንድነው የበጀኝ
ከሷ መፈጠር

ስንት ጀግና ልጆች የወደቁላት
ሴት ወንድ ሳይሉ
ክብር ያለበሷት
ደከመን ሳይሉ
ለኣእላፍ ዘመናት
ቀጥፋ በላቻቸው
ስሜት ሳይሰጣት

ምን እናት ናት ይቺ
ውለታ የማታውቅ
ዘር ማንዘሬን ሁሉ
ያስገባች ከድባቅ

ኣገር ያስደፈረች
ንብረት ያወደመች
ከኣንድ ልጇ ነጥቃ
ለኣንዱ ያስወረሰች
ዜጋ በጦርነት
በጠኔ የጨረሰች
ይችስ ጠላት እንጂ
ምኑን እናት ሆነች
ለካስ ክፉ ጨካኝ
እናት ኣገር ኣለች

ከእንዲህ ኣይነት እናት
እንዲህ ካለች ኣገር
ደስ ይለኝ ነበረ
ሳልወለድ ብቀር
ምንድነው ድርሻየ
ከስቃይ ባሻገር
ከዚች ከማትበጀኝ
ከክፉ እናት ኣገር !!

እየሩ
March 19/2024

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *